ምዘና መብት ነው!!!
በሀገራችን የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ የትምህርት ጥራትን ከማረጋጋጥ አኳያ አዋጭ ናቸው የተባሉ ስትራቴጂዎች በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ በየደረጃው ያሉ ተማሪዎቻችን የደረሱበት የትምህርት ደረጃ በሚፈቅድላቸው ልክ የሀገራቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጨባጭ ዕውነታዎች በመገንዘብ የሀገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት የሚችሉበት አቅም ሲኖራቸው ትምህርት በጥራት ስለ መሰጠቱ ማረጋገጫ አገኘን ማለት ነው፡፡
የትምህርት ጥራት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ትኩረትን የሚሻ ወሳኝ ሀገራዊ ተልዕኮ ስለ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ይህንን ተልዕኮ ከማሳካት አንፃር በየዓመቱ ካለን ውስን ሀብት ላይ ከፍተኛውን በጀት ከመመደብ ጀምሮ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ምዘና /ፈተና/ ተብሎ ከመጠራቱ ጋር በተያዘዘ በአብዛኛው ተገደን እንጂ ወደንና ፈቅደን የምንወስደው የትምህርት ስርዓቱ አካል አድርገን አናይም፡፡ ሰዎች በህይወት እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ለሚያከናውኗቸው ተግባራት መሰናክል ሲገጥማቸው “ፈተና ደረሰብኝ” በማለት ሲያማርሩ የምንሰማበት አጋጣሚ ብዙ በመሆኑ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡
ይሁን እንጂ የትምህርት ምዘና ሳይንሳዊ መነሻ ያለውና በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ለውጦች እንዲመጡ የሚያደርግ የትምህርት ሥርዓቱ አካል ነው፡፡ የመማር ማስተማሩን ሂደት ከማሳደግና ከማበልጸግ አንፃር ያለውን ወሳኝ ሚና በመገንዘብ እያንዳንዱ ተማሪ ምዘና መብቴ ነው!! መመዘን አለብኝ በማለት ጥራት ላለው ትምህርት መረጋገጥ የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት፡፡ ተማሪዎቻችን በተማሩት ትምህርት ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ለማሳየት የሚረዱ ምዘናዎች በየትምህርት እርከኑና በመማር ማስተማሩ ሂደት በመማሪያ ክፍላቸው ውስጥ በየጊዜው እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ እነዚህ ምዘናዎች የተማሪዎቹን ብቃት ለሌሎች አካላት ለማሳየት ከማገዛቸውም ሌላ ተማሪዎቹ የደረጃቸውን ሰርተፍኬት እንዲያገኙም የሚረዱ ናቸው፡፡
በየትኛውም እርከን የተማሪዎችን ዝቅተኛ የትምህርት መቀበል አቅም መሰረት አድርገው የሚዘጋጁት የትምህርት ምዘናዎችን እንደ መልካም አጋጣሚ ከመቁጠር ይልቅ እንደ አንዳች አስፈሪ ጉዳይ የማየት አጉል ባህል በልጆቻችን ህልውና ውስጥ እንዳይሰርፅ የተማሪ ቤተሰቦች ልንከላከል ይገባል፡፡ ተማሪዎቻችን የትምህርት ምዘናን እንደ መብት እስኪቆጥሩ ድረስ በግል ህይወታቸው ውስጥም ሆነ እንደ ሀገር የሚኖረውን ጠቀሜታ ደግሞ ደጋግሞ ማስገንዘብ ይኖርብናል፡፡
የትምህርት ምዘና የሚጠይቀው በተማሩት ትምህርት ዙሪያ በቂ ዝግጅት ማድረግን ብቻ እንደሆነ ሳንሰለች ልንነግራቸው ይገባል፡፡ የተማሪዎች ዝግጅት የዓመቱን ትምህርት ከጀመሩባት ደቂቃ ጀምሮ ዓመቱን በሙሉ እንዲሆን ምክር ከመስጠት ባለፈም ልንደግፋቸው በሚገባው ልክ እየደገፍናቸው ልናበቃቸው ግዴታ አለብን፡፡ የትምህርት ምዘናን የሚናፍቅና እራሱን ለመፈተሸ የሚዘገጅ ትውልድ ባለቤቶች ልንሆን ይገባል፡፡
በየደረጃው የምንገኝ ባለድርሻ አካላት ማድረግ ያለብንን አስተዋጽኦ ማበርከት ከቻልን የትምህርት ምዘናን አስከፊ የህይወት ገፅታ አድረገው የሚቆጠሩ ብኩን ዜጎችን ከማፍራት ሀገራችንን እንታደጋታለን፡፡ “ተምሬያለሁ! አውቄያለሁ! ተዘጋጅቻለሁ! መመዘን አለብኝ!” የማለት ብቃት ያላቸው ታዳጊዎች እንዲበራከቱ ሁላችንም ትኩረት ሰጥተን በትምህርት ምዘና ላይ መሥራት ያለብንን ያህል እንሥራ፡፡
ትምህርት በባህሪው እንዲለውጥ የሚጠበቀው የተማሪዎችን ዕውቀትና ክህሎት እንዲሁም አመለካካታቸውን መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ የእያንዳንዱ ተማሪ እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ለደረጃቸው የሚመጥን ስለመሆኑ ደግሞ ማረጋገጥ የሚቻለው እንደ አስፈላጊነቱ በሚሰጡ ልዩ ልዩ ምዘናዎች አማካኝነት ነው፡፡ እነዚህ ምዘናዎች ጥራት ያለው ትምህርት ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስችሉ ሳይንሳዊ መሳሪያዎች ብቻ እንጂ በተማሪዎች ላይ የተነጣጠሩ አስፈሪ ነገሮች አይደሉም፡፡
በመሆኑም የትምህርት ምዘናዎችን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በምናገኘው አጋጣሚ ሁሉ በማስረዳት ተማሪዎቻችን ብቃታቸውን የሚያረጋግጡበትን ምዘና ለመውሰድ ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግ አለብን፡፡ የትምህርት ምዘናዎች የተማሪዎች መብት እንጂ ተገደው ሳይፈልጉ የሚወስዱት እንዳልሆነ ደጋግመን ልናስገነዝባቸው ይገባል፡፡