የትምህርት ምዘና ስርዓት ወርክሾፕ ተካሄደ

የዓለም አቀፉ ትምህርት ልማት ትብብር ተቋም (Global partnership for Education (GPE) ከትምህርት ሚኒስቴርና ከኤጀንሲያችን ጋር በመተባበር የሀገራችንን የትምህርት ምዘና ስርዓት በሙከራ ደረጃ ለማስጠናት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ከጥር 21/2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራ የቆየው ጥናት ውጤት ለትምህርቱ ዘርፍ ልማት ዕቅድም ሆነ በምዘና ስርዓታችን ላይ ለሚደረጉ ማሻሻያዎች (reforms) በግብዓትነት ያገለግል ዘንድ ዛሬ ታህሳስ 2/2012 ዓ.ም የሚመለከታቸው አካላት የታደሙበት ወርክሾፕ ተካሂዷል፡፡
በወርክሾፑ ላይ የኤጀንሲው የበላይ አመራሮች፣ የዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሮች፣ የትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ ትምህርት ባለሙያዎች፣ የዩኒሴፍ ተወካይ ወ/ሮ እሌኒ ማሞ እንዲሁም ካንትሪ ዳይሬክተር የሆኑት ሚስ ዶርቲ አንዩ ተገኝተዋል፡፡
በኤጀንሲው የትምህርት ምዘና ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑትና በጥናት ቡድኑ ውስጥ አባል የነበሩት አቶ ይልቃል ወንድምነህ የጥናቱን ውጤት ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡ የቀረበውን የጥናት ሰነድ ተከትሎም በተሳታፊዎች የጥናቱ ውጤት ለ6ኛው የትምህርት ልማት ዕቅድ እንዲሁም ለአዲሱ ፍኖተ ካርታ አቅጣጫ ጠቋሚ ሆኖ ሊያገለግልና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመስራት የሀገሪቱን የምዘና ስርዓት ማሳደግ እንደሚገባው የሚገልጹ ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡ በተጨማሪም እነዚህና በተመሳሳይ የሚደረጉ የጥናት ውጤቶች በየወቅቱ ለባለድርሻ አካላት ብሎም ለመላው ማህበረሰብ በወቅቱ ተደራሽ መሆን እንደሚገባቸውና ከውጤቶቹና ከሚሰጡት የመፍትሔ ኃሳቦች በመነሳት ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችሉ ዘንድ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለማካሄድ የከፍተኛ አመራሮች ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
Analysis of National Learning Assessment Systems [ANLAS] ANLAS Ethiopia: Country Report Document