የትምህርት ስልጠና ፓሊሲያችን ከየት ወዴት? ክፍል አንድ
ክፍል አንድ
ሀገራችን ኢትዮጵያ የህዝቦቿን ኑሮ ማሳደግ የምትችለው ያላትን የሰው ሃይል አቅም በትምህርት በመገንባትና በማነፅ መሆኑን በመርዳት በ1986 ዓ.ም የትምህርትና ሥልጠና ፓሊስ በመቅረጽ ላለፉት 24 አመታት ይህን የሰው ሀብት በማልማት ሀገራችንን በአጭር ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ብሎም ከበለፀጉት አገሮች ተርታ ማሰለፍ መሠረታዊ መሆኑን በመረዳት ለትምህርትና ሥልጠና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል፡፡ ከዚህም አንፃር ፖሊሲውን መሰረት ያደረጉ የትምህርት ስታንዳርዶች ስትራቴጂዎች፣ የትምህርት ልማት መርሃ ግብሮች (ESDP I-V) የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ( ETP I እና ll) ከሀገራዊ የልማት አቅጣጫዎች ጋር በማስተሳሰርና በማዘጋጀት የትምሀርት ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነት፣ አግባብነትና ጥራትን ለማጐልበት ሰፋፊ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ከተግባራዊነቱ ጐን ለጎን የተለያዩ ስታስቲካል መረጃዎች፣ የክትትል ሪፓርቶችና ሰነዶች እንደሚያመላክቱት ከተጣለው ግብ አንፃር የአፈፃፀም ሰፊ ክፍተቶችና ተግዳሮቶች እንደነበሩበት ነው ፡፡ ከዚህም መነሻነት አሁን አላማችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ፓሊስ ማዘጋጀትና በዕቅድ መምራት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የተለያዩ ሀገራትን ልምድ መሠረት ያደረገ የትምህርት ፍኖተ-ካርታ ዝግጅት የተለያዩ ምሁራንን ያካተተ የጥናት ቡድን ተዋቅሮ የተካሄደ ሲሆን ረቂቅ ጥናቱ የመጨረሻውን ቅርጽ እንዲይዝ ለውይይት ቀርቧል፡፡
ባለፉት ሀያ አራት ዓመታት ጉዟችን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት በሁሉም የሀገራችን አከባቢዎች ለማድረስ በመቻሉ በአሁኑ ወቅት የትምህርት ተቋማት ቁጥር ከ39 ሺህ በላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና 3,3ዐዐ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ ከ28 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ማስተናገድ ተችሏል፡፡ በተሳትፎ ደረጃም የአንደኛ ደረጃ ጥቅል ተሳትፎን ከ1,114%በላይ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎውን 47.1%ማድረስ የተቻለ ሲሆን በመሰናዶ ትምህርት ከግማሽ ሚሊዬን በላይ ተማሪዎች በመማር ላይ ሲሆኑ በየዓመቱ ለከፍተኛ ትምህርት ተገቢውን ማለፊያ እያስመዘገቡ ወደ ዩኒቨርስቲ የሚገቡ ተማሪዎችን ቁጥር ከመቶ ሃምሳ ሺህ በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ዘርፍን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት በየወረዳው 1,546 የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ያሉ ሲሆን ስራ ፈጣሪ ዜጋ በማፍራትም ሆነ ለልማቱ የሚያስፈልገውን በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ ባለሙያ በማቅረብ በኩል ሥራዎች እንዲከናወኑ ያስቻሉ ናቸው፡፡ ተቋማቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግባቸው ማዕከላት ወደ መሆን እየተሸጋገሩ የሚገኙ ሲሆን አሁን በደረስንበት ወቅት ከ75 ሺ በላይ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማሸጋገር ተችሏል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፉን በተመለከተ ተቋማቱን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር መንግስት በወሰደው ፓለቲካዊ ቁርጠኝነት ቁጥራቸውን 46 ማድረስ የተቻለ ሲሆን ከዚህም ጐን ለጐን ወደ 13ዐ የሚደርሱ የግል ከፍተኛ ተቋማት በሥራ ላይ ይገኛሉ ይህ በዩኒቨርስቲያችን የማስፋፋትና የመቀበል አቅማቸውን ሀገሪቱ ላቀደችው የኢዱስትራላይዜሽን ግብ መሠረት የሚጥል መሆኑ እሙን ነው፡፡
የትምህርት ስልጠና ችግሮቻችን
ከዚህ ሁሉ ስኬታማነት በስተጀርባ የፍኖተ ካርታው እጥኚ ባለሙያዎች ባካሄዱት ዳሰሳ ከፍተኛ የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲው ያላሳካቸው ሰፋፊ ተግባሮች እንዳሉ ለማሳየት ችለዋል፡፡ በዚህም መሠረት በቀረበው ረቂቅ ውይይት ጥናት ሰነድ ላይ ከአጠቃላይ ትምህርት ጋር በተያያዘ የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ከፍተሐዊነትና ተደራሽነት አንፃር ትኩረት የተነፈገውና በአግባብቡ ያልተተገበረ ሲለው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ፕሮግራም (ከ1ኛ-8ኛ ክፍል) ፍትሐዊነትን ሙሉ በሙሉ ያላረጋገጠ ይለዋል፡፡ አያይዞም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ፕሮግራምን (11ኛ-12ኛ) በጣም አዝጋሚ ዕድገት እያሳየ ያለ ሲሆን የመሰናዶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ፕሮግራም /11ኛ-12ኛ ክፍል/ ምንም እንኳን በዕቅዱ መሰረት እየሄደ ቢሆንም ሀገራችን ካለመችው የሰው ኋይል ፍላጐት አኳያ በጣም ዝቅተኛ የተሳትፎ መጠን እንዳለው ያሳያል፡፡
የጐልማሶች ትምህርትን በተመለከተ የጥናት ሰነዱ ባለቤት አልባ በማለት የገለፀው ሲሆን እስካሁን ማንበብና መፃፍ የሚችሉ ጐልማሶችን ቁጥር 65%ማድረስ የተቻለ ቢሆንም በአንፃሩ እስካሁን 8.4 ሚሊዬን ጐልማሶች ማንበብ፣ መፃፍና ማስላት እንደማይችሉ ያሳያል፡፡
የትምህርት ብቃትና ጥራትን በተመለከተም ሰነዱ እጅግ አሳሳቢ የሆነ ብክነት የሚታይበት ብሎ ያስቀምጠዋል ከመጠነ ማቋረጥ ጋር በተያያዘም1ኛ ክፍል ከገቡ ህፃናት ውስጥ በ2ዐዐ9 እስከ 5ተኛ ክፍል የሚዘልቁ ተማሪዎች ምጣኔ 53.5%ብቻ መሆኑን በማመላከት የማጠናቀቅ ምጣኔ በተመለከተ አፈፃፀማችን ችግር እንዳለበት አመሏክቷል፡፡ የትምህርት ጥራትና አግባብነትን በተመለከተ ለ21 ኛው ክፍለ ዘመን ምላሽ የማይሰጥ እና መስተካከል ያለበት ሥርዓተ-ትምህርት ስራ የሚገልፀው ሲሆን ባለፉት 24 አመታት በትምህርትና ስልጠና ፓሊስ የተቀመጡ አላማዎችን መሠረት በማድረግ ሥርዓተ -ትምህርት በመቅረጽ የሀገሪቱን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በመደገፍ በኩል አስተዋጽኦ ያበረከተ ቢሆንም በሁሉም እርከን ያለው ስርዓተ-ትምህርት አለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን መሠረት ያላደረገ በየጊዜው እየተፈተሸ የማይከለስ፣ በተግባር ላይ ከማተኮር ይልቅ በንድፈ ሃሳብ ላይየተመሠረተ መሆኑና ለፈተና የማዘጋጀት መርህ የሚከተል መሆኑ የሥርዓተ ትምህርት ችግር መሆኑን አስቀምጧል
ከመምህራን ጋር በተያያዘ ሰነዱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ሲያስቀምጥ የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ ያልቻለ የመምህራን ምልመላና ዝግጅት ሲል ገልጾታል፡፡ እንደማሳያም ምንም እንኳን አብዛኞቹ መምህራን ለደረጃው የሚጠበቀውን የትምህርት ዝግጅት የሚያሟሉ ቢሆንም ከ2ዐዐ6-2ዐዐ9 ዓ.ም በተካሄዱ የሙያ ፈቃድ ምዘናዎች ምዘናውን ከወሰዱት 14ዐ,435 የመጀመሪያ እና 24,ዐ63 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ውስጥ የመቁረጫ ነጥቡን በሟሟላት ያለፉት 22% ብቻ መሆናቸውን ያትታል፡፡ በተጨማሪም ውጤት ግብዓትና ሂደት መስፈርት ባደረጉ የኢንስፔክሽን ስራዎች እጅግ አሳሳቢ የሆነ የትምህር ቤቶች ሁኔታ እንዳለ ያሳያል::
ከተማሪዎች ውጤት ጋር በተገናኘም የጥናት ሰነዱ የተካሄዱ የዝቅተኛ ክፍሎች የንባብ ክህሎት ምዘና፣ የዝቅተኛ ክፍሎች የሂሳብ ክህሎት ምዘና እንዲሁም በ4ተኛ፣ በ8ተኛ፣ በ10ኛ እና በ12ኛ ክፍሎች ላይ የሚደረጉ የትምህርት ቅበላ ጥናቶችን ውጤት መሰረት በማድረግ በፖሊሲው ላይ የተቀመጠውን ያላሳካ የተማሪዎች የመማር ውጤት ሲል ይገልጸዋል፡፡ ለዚህም በዋነኝነት ሚናቸውን በሚገባ ያልተወጡ የአጠቃላይ ትምህርት ባለድርሻ አካላት በማለት ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የትምህርት አመራሮች እና ወላጆች የፈጠሩትን ክፍተት በስፋት ያትታል፡፡
በመጨረሻም የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠናን በተመለከተ ረቂቅ የውይይት ጥናት ሰነዱ ፍትሐዊነትና ተደራሽነትን ያላረጋገጠ፣ የቅንጅትና የውህደት ችግር ያለበት፣ ከኢንዱስትሪው ፍላጎት ጋር ያልተሳሰረ የሙያ ደረጃ ምደባ፣ ፈጠራን የማያበረታታና ከስራ ጋር ያልተቀናጀ ሥርኣተ ትምህርት፣ ኢንዱስትሪው በእምነት ያልተቀበለው የትብብር ስልጠና እና ከኪራይ ሰብሳቢነት ያልጸዳ፣ ኢንዱስትሪው ባለቤት ያልሆነበት የሙያ ብቃት ምዘና የሚካሄድበት፣ የስልጠና ጥራትን ማረጋገጥ ያልቻለ የአሰልጣኝ ምልመላና ዝግጅት፣ በበቂ ዕውቀት ላይ ያልተመሰረተ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ውጤት ላይ ትኩረት ያላደረገና ያልተቀናጀ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ፣ በተለያዩ ችግሮች የተወሳሰበ የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና አደረጃጀት እና አመራር፣ በቂ ትኩረት ያልተሰጠው የቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና የፋይናንስ ሥርዓት ያሉበት ሲል በእያንዳንዱ ርዕስ ስር በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን ተንትኖ አስቀምጧል፡፡
ከከፍተኛ ትምህርት ጋር በተያያዘም ለሴቶች እና ልዩ ፍላጎት ላላቸው ወገኖች ትኩረት ያልሰጠ የከፍተኛ ትምህርት ፍትሐዊነት እና ተደራሽነት፣ ጥራትና አግባብነት ያላረጋገጠ የመምህራን ብቃት፣ የህብረተሰቡን ችግር ያልቀረፈ ጥናት እና ምርምር እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት፣ ብቁ ምሩቃን ማፍራት የተሳነው የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት፣ ለብክነት የተጋለጠ የዩንቨርስቲዎች ሀብት/ውስጣዊ ብቃት/፣ የትምህርት ጥራትን ያላረጋገጠ ገንዘብ መሰብሰብ ለይ ያተኮረ የግል ተቋማት ሚና እና ያልተቀናጀ የባለድርሻ አካላት ሚና (ተማሪዎች መምህራን የከፍተኛ ትምህርት አመራር) በማለት ያሎትን ክፍተቶች በጉልህ ያሳያል፡፡
ከትምህርት አመራርና አደረጃጀት ጋር በተያያዘም ከወቅቱ ጋር ያልተሳሰረ የትምህርት ፍልስፍና/ ዓላማ፣ የህጻናትን እድገት ከስራ ዓለም ጋር ያላገናዘበ የትምህርት መዋቅር፣ በቀጣይነት ራሱን እያበቃ የማይሄድ እና ለሌሎች አቅም መሆን ያልቻለ የትምህርት አመራርና አስተዳደር፣ በችግር የተወሳሰበ የሀብት አቅርቦት እና አጠቃቀም፣ ወቅታዊነት እና ተአማኒነት የጎደለው የትምህርት መረጃ ስርዓት፣ ከፖሊሲው ያፈነገጠ አተገባበር ለው መሆኑን አትቷል፡፡
ከዚህ በመነሳትም እነዚህ ግዙፍ ችግሮች ትውልዱ ከትምህርት ስልጠናው እውቀት፣ክህሎት እና አመለካከት በበቂ ሁኔታ ይዞ ከመገኘት ይልቅ የምስክር ወረቀት አምላኪ እንዲሆን እንዳደረገው እና በሂደቱም የኩረጃና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ጎልቶ እንዲታይ መሆኑ ከብዙዎቹ አንዱና ዋነኛው መሆኑን በማውሳትና ፖሊሲው ማሻሻያ እንደሚስፈልገው በማስረገጥ ስር ነቀል የማሻሻያ ሃሳቦችን ለውይይት አቅርቧል፡፡
ክፍል ሁለት
የትምህርት ስልጠና ፖሊሲ ማሻሻያ ሃሳቦች
ይቀጥላል …