የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ

ጥቅምት 29/2012 ዓ.ም በአዳማ ኩሪፍቱ ሆቴል የኤጀንሲውን አጠቃላይ አሰራርና በ2011 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ፈተና ዙሪያ ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል፡፡ በመድረኩም የቋሚ ምክር ቤቱ አባላት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ገረመው ሁሉቃ እንዲሁም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ክፍል ኃላፊዎች፣ የኤጀንሲው ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የስራ ክፍል ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
በመድረኩ በኤጀንሲው የፈተና ዝግጅትና አሰጣጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አረጋ ማማሩ ከፈተና ስራው ጋር በተያያዙ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ የሚሰጥ ሰነድ አቅርበዋል፡፡ የሀገር አቀፍ ፈተና ዋና ዋና ዓላማዎች፣ የሀገር አቀፍ ፈተና መዛኝነት፣ የመለየት ብቃትና የመለኪያ ስታንዳርዶች፣ የፈተና አዘገጃጀት ማዕቀፍ በሚል ከዝግጅት ሂደቱ ጀምሮ በፈተና ወቅት እስከሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ድረስ በዝርዝር ቀርቧል፡፡
በመቀጠል በ2011 ዓ.ም የተፈጠረውን የውጤት ግሽበት ለማጣራት በተሰየመው ኮሚቴ ውስጥ ከሰሩት አባላት መካከል አንዱ በነበሩ ባለሙያ የተካሄዱ የማጣራት ስራዎችና የተወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ በመረጃ በተደገፈ መልኩ ጠለቅ ያለ ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡
ይህን ተከትሎም የት/ሚኒስቴር ሚኒስቴር ደኤታ የሆኑት ዶ/ር ገረመው ሁሉቃ ከፈተናው ጋር በተያያዘ ተፈጥረው የነበሩት ክስተቶች አስቸጋሪ እንደነበሩ አውስተው ሆኖም በተደረገው የተቀናጀ ርብርብ ሊፈታ እንደቻለና ጎን ለጎንም ኤጀንሲው ውስጥ በእኔነት መንፈስ የሚሰሩ ጠንካራ ባለሙያዎች እንደሚገኙ የተገነዘቡበት ወቅት ሆኖ ማለፉን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በቀጣይ ኤጀንሲው አሰራሩን ለማዘመን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በጋራ የጀመራቸው ስራዎች እንዳሉ ገልጸው በዚህ ዓመት በኤጀንሲው ተዘጋጅቶ የሚሰጠው የ2ኛ ደረጃ መልቀቂያ /የ12ኛ ክፍል/ ፈተና ብቻ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም የምክር ቤቱ አባላት በመድረኩ ገለጻ መደሰታቸውንና ኤጀንሲው በቀጣይም በዚሁ መልኩ ስራውን ለምክር ቤቱ ብሎም የተለያዩ የኮሙኒኬሽን ስልቶችን በመጠቀም ለመላው ማህበረሰብ በወቅቱ ግልጽ እያደረገ መጓዝ እንደሚጠበወቅበትና የአሰራር ክፍተቶቹን በመፈተሸ በተሻለና በዘመነ ስራ መቅረብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡