የ2010 ዓ.ም የፈተና አስተዳር አፈጻጸምን የተመለከተ የምክክር መድረክ ተካሄደ

ከህዳር 13-14/2011 ዓ.ም የ2010 ዓ.ም የፈተና አስተዳደር አፈጻጸምን እና የ2011 ዓ.ም ቀጣይ አቅጣጫዎች አመላካች የሆነ የምክክር መድረክ በአዳማ አዩ ኢንተርናሽናል ሆቴል ተካሂዷል፡፡ በምክክር መድረኩ የክልል ት/ም ቢሮ ፣ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የጸጥታ እና አስተዳደር ጉዳይ ኃላፊዎች፣ የሙያ እና ድጋፍ ሰጪ ማህበራት ተጠሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተውበታል፡፡
መድረኩ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ አርዓያ ገ/እግዚአብሄር የመክፈቻ ንግግር የተጀመረ ሲሆን በመቀጠል የ2010 ዓ.ም ፈተና አስተዳደር አፈጻጸም እና የ2011 ዓ.ም አቅጣጫ አመላካች በሚል የተዘጋጀው የመወያያ ሰነድ የፈተና ዝግጅት እና አሰጣጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ አረጋ ማማሩ ለተሳታፊው ቀርቧል፡፡
ሰነዱ ሦስት ዋና ዋና ዓላማዎችን የያዘ ሲሆን እነዚህም የ2010 የፈተና እስተዳደር አጠቃላይ አፈጻጻም፣ የ2011 ዓ.ም የፈተና ስራ አስፈጻሚዎች ምልመላ ግልጸኝነት እንዲሁም ከአዲሱ ፍኖተ ካርታ ጋር በተያያዘ ያለ የመረጃ ክፍተትን ማጥራት መሆኑን አቶ አረጋ ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሰረት የፈተና አስተዳደሩን በተመለከተ በቅድመ ፈተናው የፈተና ዝግጅት፣ የተፈታኝ ምዝገባና የምዝገባ ጣቢያዎች መረጃ፣ ህትመትና ስርጭት፣ የፈተና አስፈጻሚ ምልመላና ስምሪት፤ በፈተና ወቅት የፈተና ደህንነትና አሰጣጥ እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም በድህረ ፈተናው የመልስ ወረቀት ርክክብ፣ የፈተና አስፈጻሚዎች ክፍያ፣ እርማት እና የመልስ ቁልፍ፣ የፊደልና የደረጃ መቁረጫ ነጥብ አወሳሰን፣ የፈተና ደንብ ጥሰት ማጥራትና ውሳኔ መስጠት ብሎም ውጤት መግለጽ በሚል ተከፋፍሎ በሰፊው ቀርቧል፡፡
በተያያዘ መልኩ የ2010 ዓ.ም አጠቃላይ የፈተና ዝግጅቱን፣ የተነሱ ቅሬታዎችንና ውጤትን በተመለከተ እንዲሁም በፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ወቅት የተከሰቱ የፈተና ስርቆት ሙከራ፣ ሞባይል ስልክ ይዞ ወደ መፈተኛ አዳራሽ መግባት፣ ለሌላ ሰው መፈተን ፣ ለፈተና ስራ የተሰማሩ አካላትን ማስፈራራት እና የመሳሰሉት ባጋጠሙ ችግሮች ስር የቀረቡ ሲሆን ለቀጣይ መሻሻሎች ምክረሃሳቦችም ተሰንዝረዋል፡፡
ከአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጋር በተያያዘም በምሁራን በተደረገ ጥናት መሰረት ረቂቅ ሰነዱ ለህዝብ ውይይት የቀረበበት ሁኔታ እንዳለና በውይይት ከዳበረ በኋላ ወደ ትግበራው የሚገባ ሲሆን በረቂቅ ሰነዱ ላይ ያሉትን ምክረሃሳቦች መሰረት በማድረግ ዘንድሮ የ10ኛ ፈተና አይኖርም የሚሉና የመሳሰሉ በህብረተሰቡ ዘንድ ግራ የሚያጋቡ ሃሳቦች እንዳሉ ሆኖም ፍኖተ ካርታው ጸድቆ የስርዓተ ትምህርት ለውጥ ተካሂዶ ስራ ላይ ባለመዋሉ አሁን ያለው ሂደት ባለበት ሁኔታ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
በመቀጠል በኤንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገ/እግዚአብሄር፣ በም/ዳይሬክተሮቹ ዶ/ር ዘሪሁን ዱሬሳ እና አቶ መሳይ ደምሴ አወያይነት የመድረኩ ተሳታፊዎች በቀረበው ሰነድ ዙሪያ በርካታ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ሰንዝረዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ለፈተና ስራ አስፈጻሚዎች ሊደረግ ስለሚገባው የክፍያ ማሻሻያና የፈተና ጉዳይ ማስፈጸሚያ በጀት በወቅቱ ማድረስ፣ በፈተና ስርጭት ወቅት የሚኖሩ የፈተና መለዋወጦች እና የቅጻ ቅጽ እጥረቶችን ማስወገድ፣ በፈተና ኩረጃ እና ደንብ ጥሰት ዙሪያ ሊሰራ ስለሚገባው ጠንከር ያለ ስራ፣ እንዲሁም የመልስ ወረቀት ከውጪ ሀገር ዘግይቶ መግባት ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የተፈታኞች ምዝገባ መዘግየትን በመቅረፍ አስፈላጊነት ላይ የሰጡት አስተያየቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ለተሰነዘሩት ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት እንዲሁም አስተያየቶቹ ለቀጣይ ስራዎች እንደግብዓትነት ተወስደው እንደሚሰራባቸው ከመድረኩ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በኤጀንሲውን የፈተና አስተዳደር የተከለሰ መመሪያ ላይ ለግብዓትነት የሚሆኑ ኃሳብ እና አስተያየቶችን በኢሜል ለኤጀንሲው የህግ ክፍል እንዲልኩ አቅጣጫ ተሰቷል፡፡
በመጨረሻም በ2010 ዓ.ም በተሰጠው የ2ኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ሰርተፍኬት ፈተና /የ10ኛ ክፍል/ እና የዩንቨርስቲ መግቢያ ፈተና /የ12 ክፍል/ ፈተናዎች ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል እጅግ በጣም ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ከየትምህርት ደረጃው ሦስት በአጠቃላይ ለስድስት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተሰቷል፡፡

















