ከውድቀታችን ላለመማር …

ለሀገራዊ ግብ ስኬት በራሱ የሚተማመን ዜጋ ማፍራት ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መሠረቱ ትምህርት ነውና ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰፍን በሁሉም መስክ የተሰማራን የሀገራችን ጉዳይ ግድ የሚሰጠን ዜጎች በሙሉ ልንረባረብ ይገባል፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት ለእያንዳንዱ ዜጋ እንዲዳረስም በትምህርት ተቋማት ተግባራዊ እየተደረጉ ካሉት ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ሁሉም ባለድርሻ ማድረግ ያለበትን አስቦ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡ ከአፀደ ህፃናት ጀምሮ ተማሪዎቻችን እንዴት እየተማሩ እንደሆነ ለመከታተል የግዴታ ወላጅ ወይንም መምህራን መሆን የለብንም የዜግነት ግዴታችን ሊሆን ይገባዋል፡፡

በትምህርት ዓለም ያሉ ተማሪዎቻችን አብዛኞቹ የታላላቆችን ክትትል በየደረጃው የሚፈልጉበት እድሜ ክልል ላይ ስለሚሆኑ በአስተሳሰባችንም ሆነ በተግባራችን በጎ ተፅዕኖ ለመፍጠር አስበን ሠላማዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ታዳጊዎቻችንን መንከባከብ አለብን፡፡ ከተራ ንግግሮቻችን ጀምሮ በታዳጊዎቻችን ዙሪያ የምንፈፅማቸው ድርጊቶቻችን በህፃናቶቻችንና በተማሪዎቻችን ላይ ምን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ማስተዋል ይጠበቅብናል፡፡

በተለይም የዛሬ ታዳጊ ተማሪዎቻችን በሙሉ የነገ ሀገር ተረካቢ ስለመሆናቸው ለሰከንድም ሳንዘነጋ ሀገራችንን በአስተማማኝ መዳፍ ላይ ለማስቀመጥ አልመን ጥራት ባለው ትምህርት መታነፃቸውን እያረጋገጥን ልንጓዝ ይገባል፡፡ ጥራት ላለው ትምህርት መለኪያ ከሆኑት መንገዶች መካካል አንዱ ምዘና ነውና ተማሪዎቻችን በየደረጃው የሚሰጧቸው ፈተናዎች ውጤት ላይ ብቻ ሳይሆን አሠራራቸውን በመፈተሽ መደገፍ የሚገባን ቦታ ላይ ልንደግፋቸው ይገባል፡፡ የትምህርት ምዘናዎች በየደረጃው የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው፡፡
በየደረጃው የሚሰጡ የትምህርት ምዘናዎች (ፈተናዎች) ተማሪዎች በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ የተቀረጹትን ግቦች ዕውን ለማድረግ የተቀመጡ የትምህርት ይዘቶችን በምን ያህል ደረጃ እንዳወቋቸው፣ እንደተረዷቸውና ሊተገብሯቸው እንደቻሉ ለማወቅ የሚረዱ ስልቶች ናቸው፡፡ የሚመለከታቸው የትምህርት ባለድርሻ አካላት ከትምህርት ምዘናዎች ውጤት በመነሳት ከዝቅተኛው የማስተማር ስልት ጀምሮ ፖሊሲ ለመለወጥ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን እስከማሳለፍ የሚደርሱበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህም ከትምህርት ዘመኑ መጀመሪያ ጀምሮ የዓመቱ ትምህርት እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ልጆቻችን ተምረው በአካላቸው፣ በአስተሳሰባቸው በተለይም በስነ ምግባራቸው የተገኙትን ለውጦች እየፈተሸን መሄድ ይጠበቅብናል፡፡

ትምህርት ቤቶቻችን የልጆች መዋያ ሳይሆኑ ሀገር ተረካቢ ዜጎች ማፍሪያ እንደሆኑ አስበን ልናደራጃቸውና ልንጠብቃቸው ይገባል፡፡ ስለሆነም የሚመለከተን ሁሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ‘’ውለው ይምጡ‘’ ማለታችንን አቁመን ያካበቱትን የዕለት ከዕለት ለውጥ፣ የሚጓዙበትን አቅጣጫ ትክክለኛነት እያረጋገጥን መሄድ ግዴታችን ነው፡፡
ተማሪዎቻችን ሲማሩም ሆነ ሲፈተኑ የሥነ-ምግባር ግድፈቶች እንዳይታይባቸው መጠበቅ የሁሉም አካል ግዴታ ነው፡፡ አጥፍተው እንኳን ቢገኙ የማስተካከል ኃላፊነቶች የሚወድቁት በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ ሊሆን ይገባል፡፡

በሀገራችን በተጨባጭ እንደሚስተዋለው የፈተና ደንብ ጥሰት በተለይም የፈተና ኩረጃ ከላይ እስከታች ድረስ ባሉ የትምህርት ተቋማቶቻችን ውስጥ ከምናስበው በላይ በፍጥነት እየተዛመተ የሚገኝ የትምህርት ጥራት ነቀርሳ ነው፡፡ አንድ ተማሪ በኩረጃ ብቻ ከአንደኛው የትምህርት እርከን ወደ ሌላው የትምህርት እርከን እየተሻገረ አገልጋይ የሚሆንበት ደረጃ ላይ ቢደርስ ከሚሰጠው በጎ አገልግሎት ይልቅ የሚያበላሸው እንደሚበዛ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ተገልጋዮች ደግሞ እኛው ነንና ባበላሸነው መንገድ ተጉዘው የዘራነውን መጥፎ አዝመራ ከሚያሳጭዱን የነቀዙ ፍሬዎች እራሳችንን ለመከላከል የምንችለው ዛሬ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ በእጃችን ላይ ያለውን ጊዜ ተጠቅመን ማስተካከል የሚኖርብንን ሳናስተካከል ከቀረን ዋጋ እምንከፍለው ለዘመናት እንደሚሆን መሸፋፈን አይኖርብንም፡፡

ልጆቻችንን አውቀናቸውና ተረድተናቸው ሳይጣመሙ እንዲበቅሉ እናግዛቸው እንጂ በነሱ ባልሆነ ዋጋ እየኮሩ እንዲያድጉ አናለማምዳቸው፡፡ በትምህርት አለምም ይሁን በተለምዶ ህይወት ውስጥ የሚኮሩበት ነገር በሙሉ የራሳቸው የድካም ውጤት እንደሆነ እያረጋገጥናላቸውና በራሳቸው ልክ ብቻ እንዲጓዙ እያገዝናቸው መሄድ ይጠበቅብናል፡፡ በራስ ማንነትና በተኮረጀ ስብዕና ውስጥ የሚገኙትን ልዩነቶች ጠንቅቀው እያወቁ እንዲያድጉ መንገር፣ ማስተማርና ማሳወቅ የሚጠበቅብን እኛው ነን፡፡ የተኮረጀ ነገር በሙሉ ጊዜያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ብቻ ከመንገር ባለፈም ከግለሰብ ጥፋት እስከ ሀገር ማፍረስ የሚደርስ ዋጋ እንደሚያስከፍል እኛም በአግባቡ ገብቶን ለታናናሾቻችን በጥልቀት እንዲረዱት ማድረግ አለብን፡፡ ማድረግ የሚጠበቅብንን ነገር በሙሉ ሳናደርግ ጊዜዎቻችን ቢያልፉ ውድቀታችን እንደ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት ዋጋ የሚከፈልባቸው ችግሮችን እያካበትን ነው የምናልፈው፡፡ በመሆኑም ወድቀን ለመነሳት ከመቸገራችን በፊትና ከውድቀታችን ለመማር ከምንሞክር ዛሬ ላይ ማድረግ ያለብንን ጠንቅቀን እናከናውን፡፡