የ2010 ዓ.ም የ10ኛ ክፍል እና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የምዝገባ አፈፃፀም

 1. ለምዝገባ የሚያበቁ ሁኔታዎች

የኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና (10ኛ ክፍል) ለመመዝገብ፣

 • መደበኛ ተማሪዎች

የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው የተዛወሩና በትምህርት ሚኒስቴር ወይም በክልል ትምህርት ቢሮ ዕውቅና በተሰጣቸው ትምህርት ቤቶች በቀጣዩ ዓመት 9ኛ ክፍል አጠናቀው በ2010 ዓ.ም 10ኛ ክፍል በቀን ፕሮግራም በመማር ላይ የሚገኙ ሲሆን ዓመቶቹ ተከታታይ መሆን አለባቸው፡፡

 • የማታ ተማሪዎች

የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው የተዛወሩና በትምህርት ሚኒስቴር ወይም በክልል ትምህርት ቢሮ ዕውቅና በተሰጣቸው ትምህርት ቤቶች በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት 9ኛ እና 10ኛ ክፍልን በሦስት ዓመት ተምረው ለማጠናቀቅ በ2010 ዓ.ም በማታ ፕሮግራም የ10ኛ ክፍል ትምህርት የአንደኛ ሴሚስተር ውጤት የሚገልጽ ትራንስክሪፕት ማቅረብ የሚችሉና በመማር ላይ የሚገኙ፣

 • የግል አመልካቾች
 • በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና ወይም በቀድሞው ሥርዓተ ትምህርት የኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ፈተና (ESLCE) በመደበኛ ወይም በማታ ወይም በግል የተፈተኑበትን ሠርቲፊኬት ማቅረብ የሚችሉ፣
 • የኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና ለመውሰድ የሚያመለክቱ ተመዝጋቢዎች በተፈተኑበት ዓመት ለመሰናዶ የተቆረጠውን የማለፊያ ነጥብ ያላመጡ መሆን አለባቸው፡፡
 • የርቀት ትምህርት ተከታትለው የኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ (10ኛ ክፍል) ፈተና በግል ለመውሰድ የሚፈልጉ የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው የተዛወሩና ዕውቅና ከተሰጠው የርቀት ትምህርት ተቋም የ9ኛ ሦስት ሴሚስተር እና የ10ኛ አንድ ሴሚስተር የትምህርት ማስረጃ (ትራንስክሪፕት) እና የድጋፍ ደብዳቤ ከ8ኛ ክፍል ሠርቲፊኬት ጋር በአካባቢው ለሚገኘው የወረዳ ምዝገባ ጣቢያ በማቅረብ መመዝገብ ይችላሉ፡፡

የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ለመመዝገብ፣

 • መደበኛ ተማሪዎች

የኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ሠርቲፊኬት (EGSECE) ፈተና ተፈትነው በወቅቱ የነበረውን የማለፊያ ነጥብ በማምጣት የ11ኛ ክፍል ትምህርት አጠናቀው በ2010 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል በመማር ላይ ያሉ ሲሆን ዓመቶቹ ተከታታይ መሆን አለባቸው፡፡

 • ለማታ የመሰናዶ ተማሪዎች

የማታ ክፍለ ጊዜ የመሰናዶ መርሃ ግብር ተከታትለው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ለመቀበል የሚያመለክቱ ተመዝጋቢዎች የ10ኛን ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና (EGSECE) በመቀበል ለመሰናዶ መርሐ ግብር የሚያበቃ ውጤት በማምጣት የ11ኛ እና 12ኛ ክፍልን በሦስት ዓመት ተምረው ለማጠናቀቅ በ2010 ዓ.ም በማታ ፕሮግራም በመከታተል ላይ ያሉ፣ ለዚህም የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ሠርቲፊኬት፣ የ11ኛ ክፍል ያጠናቀቁበትን እና የ12ኛ ክፍል የአንደኛ ሴሚስተር ውጤት የሚገልጽ ትራንስክሪፕት ማቅረብ የሚችሉ፣

 • ለግል የመሰናዶ ተማሪዎች

የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በግል ፈተናውን ለመውሰድ የሚያመለክቱ ተመዝጋቢዎች በተፈተኑበት ዓመት የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ማለፊያ ነጥብ ያላመጡና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያልተደለደሉ ብቻ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ሠርቲፊኬት በማቅረብ ሊመዘገቡ ይችላሉ፡፡

 1. የመመዝገቢያ ቦታ
 • የ10ኛ ክፍል እና የመሰናዶ (12ኛ ክፍል) መደበኛ እና የማታ ተማሪዎች የሚመዘገቡት በ2010 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በመማር ላይ ባሉበት ትምህርት ቤት ይሆናል፡፡
 • የኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ሠርቲፊኬት እና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የግል አመልካቾች ምዝገባ የሚካሄደው በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኘው የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሲሆን የአዲስ አበባ የግል አመልካቾች በሚኖሩበት ክፍለ ከተማ በሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ባሉባቸው የወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤቶች ወይም ጽ/ቤቱ በሚያዘጋጀው ምዝገባ ጣቢያ ይሆናል፡፡
 1. የመመዝገቢያ ጊዜ
 • የኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ሠርቲፊኬት እና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ምዝገባ ከጥር 28 – የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ባሉት የሥራ ቀናት በሥራ ሰዓት ብቻ ይሆናል፡፡
 1. የክፍያ አፈፃፀም
 • ወደፊት የሚገለጽ ይሆናል፡፡

የ10ኛ ክፍል ተመዝጋቢዎች

 • ከዓይነ ሥውራን በስተቀር መደበኛ ተመዝጋቢዎች ሁሉ ለኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና አማርኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ሂሳብ፣ ፊዚከስ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ሥነ-ዜጋ፣ ጂኦግራፊና ታሪክ የመመዝገብና የመፈተን ግዴታ አለባቸው፡፡ ለዓይነ ሥውራን አማርኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ባዮሎጂ፣ ሥነ-ዜጋ፣ ጂኦግራፊና ታሪክ ናቸው፡፡
 • የግል ተመዝጋቢዎች እንግሊዝኛና ሂሳብን ጨምሮ ዘጠኝ የትምህርት ዓይነቶች የመመዝገብና የመፈተን ግዴታ አለባቸው፡፡

የመሰናዶ ተመዝጋቢዎች

 • የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ማንኛውም መደበኛ፣ የማታና የግል ተመዝጋቢ ከዓይነ ሥውራን በስተቀር እንግሊዝኛና ሂሳብን ጨምሮ የትምህርት መስኩ የሚጠይቀውን ሰባት የትምህርት ዓይነቶች የመመዝገብና የመፈተን ግዴታ አለባቸው፡፡ ለዓይነ ሥውራን እንግሊዝኛ፣ ስኮላስቲክ አፕቲትዩድ፣ ጂኦግራፊ፣ ታሪክ፣ ኢኮኖሚክስና ሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ናቸው፡፡
 1. ለምዝገባ የሚቀርቡ የትምህርት ማስረጃዎች ስርዝ ድልዝ የሌለባቸው ዋና /ኦሪጅናል/ ሆነው በተለጠፈው ፎቶግራፍና በትምህርት ማስረጃው ላይ መኖር የሚገባቸው ማህተሞችና የኃላፊ ፊርማና ቲተሮች በግልጽ የሚነበቡ መሆን አለባቸው፡፡
 2. መደበኛ፣ የማታም ሆነ የግል ተመዝጋቢዎች መጠናቸው 3 X 4 ሴ.ሜ.፣ ጥራታቸውን የጠበቁ፣ ፊት ለፊት (ሁለት ጆሮዎች የሚታይ) እና ከአንድ ዓመት ወዲህ የተነሱት ጉርድ ፎቶግራፍ ለምዝገባ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ቆብ፣ ባርኔጣ፣ ሻሽ፣ የፀሐይ መነጽር አድርገው የተነሱት ፎቶግራፍ ለምዝገባ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ በሃይማኖት ምክንያት ከሆነ ብቻ ሙሉ ፊትንና ሁለት ጆሮን የሚያሳይ ፎቶግራፍ መሆን ይችላል፡፡ በፎቶግራፍ ጀርባ ላይ ስም፣ የአባትና የአያት ስም በአማርኛና በእንግሊዝኛ በግልጽ መጻፍ አለበት፡፡ ይህም ስም በምዝገባ ፎርሙ ላይ ከሚሞላው ስም ጋር አንድ ዓይነት መሆን አለበት፡፡
 3. ስለመመዝገቢያ ቅጽ አሞላልና አጠቋቆር የወጣውን ዝርዝር መመሪያ በምዝገባ ጣቢያ በመገኘት ሳይመለከቱ ቀርተው በቅጽ አሞላል ወይም አጠቋቆር ላይ አንዳች ስህተት ቢፈጠር ምዝገባው ውድቅ እንደሚሆን እና ለዚህም ኤጀንሲው የማይጠየቅ መሆኑን አመልካቾች በቅድሚያ ሊያውቁት ይገባል፡፡
 4. የስም ለውጥ ለማድረግ የሚፈልጉ ተመዝጋቢዎች ከምዝገባ በፊት ስማቸውን በሕግ አስቀይረው የተፈቀደበትን የፍርድ ቤት ማስረጃ በምዝገባ ወቅት በማቅረብ ምዝገባቸውን በአዲሱ ስም መፈጸም ይችላሉ፡፡ ምዝገባ ከተፈጸመ በኋላ የሚቀርቡ ማናቸውም ዓይነት የስም ለውጥ ጥያቄዎች ኤጀንሲው አያስተናግድም፡፡
 5. ግዕዝ፣ ፈረንሣይኛ፣ እና ሌሎች የብሔር ብሔረሰብ ቋንቋዎች ፈተናዎችን በኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ሠርቲፊኬት ፈተና በመደበኛነት ለመፈተን የሚያመለክቱ ሁሉ ትምህርቱን እንዲያስተምሩ ዕውቅና ከተሰጣቸው ት/ቤቶችና ክልሎች በመደበኛ ትምህርት ቤት በ9ኛ እና 10ኛ ክፍል ቋንቋውን ለመማራቸው ማስረጃ ማቅረብ አለባቸው፡፡
 6. ግዕዝ፣ ፈረንሣይኛ፣ እና ሌሎች የብሔር ብሔረሰብ ቋንቋዎችን በግል ለመመዝገብ የሚችሉት ቋንቋውን እንዲያስተምሩ ዕውቅና በተሰጣቸው ትምህርት ቤቶች የ8ኛ ክፍል አጠናቀው የ9ኛና የ10ኛ ክፍል ኦሪጅናል ትራንስክሪፕትና በነዚህ ቋንቋዎች ውጤት የተመዘገበበትን ሠርቲፊኬት ከአንድ ፎቶ ኮፒ ጋር በማቅረብ ሊመዘገቡ ይችላሉ፡፡
 7. የግል አመልካቾች በግንባር ወይም በሕጋዊ ተወካዮቻቸው አማካኝነት ለመመዝገቢያ ለየትምህርት ዓይነቱ የሚደረገውን ክፍያና አስፈላጊውን የትምህርት ማስረጃዎች አሟልተው በማቅረብ ሊመዘገቡ ይችላሉ፡፡
 8. ከምዝገባ መመሪያ ውጪ የተፈጸመ ምዝገባ በማንኛውም ወቅት ሲታወቅ የሚሰረዝ ሲሆን፣ ለአገልግሎት የተከፈለው ገንዘብ ተመላሽ አይሆንም፡፡ ስለዝርዝር የምዝገባ አፈፃፀም እና የምዝገባ ፎርም አሞላል ምዝገባ ጣቢያዎች በመሄድ መረዳት ይቻላል፡፡

 

ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ

የስልክ ቁጥር             011-1-232874

                             011-1-232889

                             011-1-232878