… ምዘና 2010

አንድ ገበሬ መሬቱን ከማረስ ሂደት ጀምሮ ዘር ዘርቶ ፍሬውን እስከ ሚያጭድ ከስር ስሩ እያረመ ከመሄድ ጀምሮ ብዙ ስራ እንዳለበት ሁሉ ፍሬ አፍርቶ ምርቱን በሚሰበስብበት ወቅት የሚሰማው እርካታ ማንም ሊገምተው የሚችለው ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ተማሪም ጠዋት ማታ በትምህርት ገበታው ላይ በመገኘት በመከታተል ከስር ስር ጥናቱን በማጠናከር በሚያመጣው ውጤት ፍሬያማነት መደሰቱ የተለመደ ክስተት ነው፡፡
በሁለቱም ወገን ታዲያ ውጤታማነታቸው የሚለካው በቀን ተቀን ስራቸው በሚያደርጉት ትጋት ይሆናል፡፡ ይኸውም ገበሬው ዘሩን ከመዝራት ጀምሮ ተከታትሎ ማረሙ ለፍሬያማነት እንዲያበቃው ሁሉ ተማሪውም በትምህርት ገበታው ያለው ትጋትና ትምህርቱን ሳይታክት ማጥናቱ ለስኬታማነቱ መሠረት ነው፡፡ ገበሬው በስተመጨረሻ ፍሬውን ከገለባው አንደሚለየው ሁሉ የትምህርት ምዘናውም /ፈተናም/ እንዲሁ በተመሣሣይ ሁኔታ ስኬታማ የሆነውን ተማሪ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ያሸጋግራል፡፡
ምዘና/ፈተና ተማሪዎች የተማሩትን ትምህርት በምን ያህል ደረጃ ተረድተውታል የሚለውን ለመዳሰስ የሚደረግ አንድ የትምህርት ሂደት አካል ነው፡፡ ምዘናዎች/ፈተናዎች የተለያየ ዓይነት ይዘትና መጠን እንዳላቸው የሚታወቅ ሲሆን ከነዚህ መካከል የሆኑትና የብዙሃኑን ትኩረት የሚስቡት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጡት ብሄራዊ ፈተናዎች ናቸው፡፡
በሀገራችን ኢትዩጵያ እነዚህ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጡት ምዘናዎች/ፈተናዎች ሶስት ዓይነት ናቸው፡፡ እነዚህም የ10ኛ ክፍል ወይም የኢትዮጵያ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ሰርተፍኬት ፈተና የ12ኛ ክፍል ወይም የዩንቨርስቲ መግቢያ ፈተናዎች እና የ8ኛ ክፍል ወይም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተናዎች ናቸው፡፡ ከነዚህ ሀገር አቀፍ ብሄራዊ ፈተናዎች መካከል የ10ኛ ና የ12ኛ ክፍል ፈተናዎች በኤጀንሲያችን አዘጋጅነትና አስተዳዳሪነት የሚሰጡ ሲሆኑ የ8ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በክልሎች አዘጋጅነትና አስተዳዳሪነት የሚሰጡ ናቸው፡፡
እነዚህ በየአመቱ እየተዘጋጁ ተማሪዎችን ከአንዱ ደረጃ ወደ ሚቀጥለው የትምህርት ደረጃ የሚያሸጋግሩ ብሄራዊ ፈተናዎች በተለያዩ ዓመታት የተለያዩ ቁጥር ላላቸው ተማሪዎች በጥራት ተዘጋጅተው በኤጀንሲያችን ተደራሽ ይደረጋሉ፡፡
በዚህም መሰረት በዘንድሮ የትምህርት ዓመትም እንዲሁ 1,200,676 የ10ኛ እንዲሁም 284,310 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ ምዝገባ አካሂደው ፈተናውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ብሄራዊ ፈተናዎች በወጣው መርሃ ግብር መሠረት ከግንቦት 22 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለ7ተከታታይ የሥራ ቀናት ማለትም ከግንቦት 22 እስከ 24/2010 ዓ/ም ድረስ የ10ኛ ክፍል፣ ከግንቦት 27 እስከ 30/2010 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል እንዲሁም ከሰኔ 05 እስከ ሰኔ 07/2010 ዓ/ም የ8ኛ ክፍል ሆኖ ይሰጣሉ፡፡
በመሆኑም ኤጀንሲያችን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በላቀ መልኩ በመወጣት ላይ የሚገኝ ሲሆን ስራውን ከዳር ያደርስ ዘንድ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካለትና መላው ህብረተሰብ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በመወጣት የየራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርባቸዋል፡፡
በሥራው ሂደት ዋነኛ ትኩረት የሆኑት ተማሪዎች ደግሞ ይህ ወቅት ባሳለፏቸው የትምህርት ጊዜያት የቀሰሙት ዕውቀትና ክህሎት የሚለካበትና ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አመላካች የሆነ መመዘኛ መሆኑን በመገንዘብ ስነ-ልቦናዊ ዝግጅት በማድረግና የራስ መተማመናቸውን በማጎልበት ከበቂ ዝግጅት ጋር ሊታደሙት ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ታዲያ ጎን ለጎን አጅግ ትኩረት ሊሰጡበት የሚገባ ጉዳይ የፈተና ደንብ ጥሰት/የፈተና ኩረጃ እጅግ አሳፋሪና ራስን መግደያ መሳሪያ መሆኑን በመረዳት ሊፀየፉትና ከተግባሩም ራሳቸውን ለማሸሽ ከራሳቸው ጋር ቃል ሊገባቡ ይገባል፡፡ በተጨማሪም ራሳቸውን ከዚህ አስነዋሪ ተግባር ከማራቅ በዘለለ ለሌሎችም በማስተጋባት የምዘና/የፈተና ሥርዓቱ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ይጠናቀቅ ዘንድ መልዕክቶቻቸውን በሰፊው ሊያስተጋቡ ይገባል፡፡

መልካም የዝግጅት ጊዜ!!!