ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ በሀገር አቀፍ ፈተናዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላትጋርየምክክር መድረክ አካሄደ

ሚያዝያ 20/2010 ዓ.ም በሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አዘጋጅነት በቢሾፍቱ ከተማ በፈተና ዝግጅትና አሰጣጥ ዙሪያ የውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡በውይይት መድረኩ ላይ ከተለያዩ ክልሎችየተጋበዙ የትምህርት ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ፈተናው ከማዘጋጀት ጀምሮ ለተፈታኞቹ የፈተና ውጤት እስከሚገለፅበት ጊዜ ድረስ ያሉትን ችግሮችና መፍትሄዎቻቸውን ጭምር ተወያይተዋል፡፡

ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ደረጃቸውን የጠበቁ ፈተናዎችን በማዘጋጀትና በመስጠት እንዲሁም ተገቢ የሆኑ የትምህርት ምዘናዎችን በተከታታይ በማካሄድ የትምህርት ጥራት ያለበትንደረጃ በማመላከት ለውሣኔ ሰጪ አካላት በማቅረብ ላይ ይገኛል። ይህ ሥራም በተደራጀና ሁሉንም የባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ኤጀንሲው በተደረገው ውይይት አፅንኦት ተሰጥቶታል፡፡

በ2010 የትምህርት ዘመን 1,200,676 የ10ኛ እና 284,312 የ12ኛ ክፍል ተፈታኞ የተመዘገቡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 883,555 የ10ኛ እና 243,982 የ12ኛ መደበኛ ተማሪዎች ናቸው፡፡በ2010 የትምህርትዘመን 2,850 የ10ኛ ክፍል እና 1,200 የሚሆን የ12ኛ ክፍል የፈተና ጣቢያዎች ይኖራሉ፡፡ ከግንቦት 22 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የሚሰጠው የአጠቃላይ ትምህርት ማጠናቀቂያና የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናለ7 የሥራ ቀናት የሚሰጥ ሲሆን ከ50,774 በላይ የትምህርት ባለሙያዎች በፈተና ጣቢያ ኃላፊነት በሱፐርቫይዘርነት እንዲሁም በፈታኝነት ይሰማራሉ፡፡

በሌላም በኩል የፈተናውን ደህንነት ከወትሮው በተሻለ መልኩለማስጠበቅ የፈተና ደህንነት ስራው ተጠናክሮ የሚሰራ ሲሆን በፈተና ፋይናንስ አስተዳደር ላይ በደጋፊነትየሚሰማሩከ20,000 በላይ የክልል ፋይናንስ ባለሙያዎች እንዲመደቡ ይደረጋል፡፡

በመሆኑም ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ንቅናቄን በመፍጠር ከዚያ በፊት ይከሰቱ የነበሩትን ከፈተና ዝግጅት፣ ህትመት፣ ስርጭትና ከፈተና አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ዳግም ሳይከሰቱ ሰላማዊና በተረጋጋ ሁኔታፈተናውን መስጠት ለማስቻል ከወትሮው የተለየ ዝግጅት ያካሄደ መሆኑን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ለምክክር ጉባኤው ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡