የትምህርት ምዘና የትምህርት ስርዓቱ አካል…

ሀገራችን በሁሉም መስክ የምታደርጋቸውን የልማት ግስጋሴዎች ከማገዝ አንፃር ትምህርት ያለውን የማይተካ ሚና በአምስተኛው የትምህርት ልማት ዕቅድ (ESDP5) ከተቀመጡት ልዩ ልዩ ስትራቴጂዎች ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ በተለይም የትምህርትን ፍትሀዊነትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ የተሄደበት መንገድ ያለውን አዋጭነት ስንመለከት በወቅቱ የትምህርት ስርዓቱ ተግዳሮት የሆነውን የጥራት ጉዳይ መልክ ለማስያዝ መረባረብ እንደሚገባ እሙን ነው፡፡ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ያስችላሉ ተብለው ከተነደፉ ስትራቴጂዎች መካካልም አንደኛውና ዋነኛው የትምህርት ምዘና ነው፡፡ በ1986 ዓ.ም ተቀርፆ ሥራ ላይ የዋለው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲያችን የትምህርትን ጥራት ከማረጋገጥ አንፃር የትምህርት ምዘና የሚኖረውን ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ ያስረዳል፡፡ 
የትምህርት ምዘና በተለምዶ ‘’ፈተና’’ ተብሎ ከመጠራቱ ጋር ተያይዞም የተነቃቃ ስሜት በማህበረሰቡ ውስጥ አይፈጥርም፡፡ ከልምድ ይዘነው በመጣነው አስተሳሰብ ፈተና ሲባል ከህይወት ውጣ ውረድ ጋር እየተያያዘ በጎ ያልሆኑ የህይወት ተሞክሮዎቻችን ብቻ የሚብራሩበት ቃል ነው፡፡ ሰዎች በተለያየ መንገድ በህይወታቸው ውስጥ ያሰቡት ስኬት ሲርቃቸው፣ እንዳሰቡት አልሆን ሲላቸውና በመንገዳቸው ላይ መሰናክል ሲበዛባቸው ‘’ፈተና ገጠመኝ’’ በሚል ሲያማርሩ እናገኛቸዋለን፡፡ ከዚህ መነሻም በትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚሰጠው ፈተና በአብዛኞቻችን እንደ አንዳች አስፈሪ ነገር፣ ከድካም፣ ከእንግልትና ከስቃይ ጋር አብሮ በመታሰቡ ምክንያት ፍትት ያለ የደስታ ነጻ ስሜት የሚፈጥርበት ሁኔታ ብዙ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ፈተናን/ምዘና/ ጠቅለል አድርገን ለመረዳት ስንሞክር የትምህርት ሥርዓቱ ተማሪዎች የተማሩትን ትምህርት በምን ያህል መጠን እንደተረዱት ዕውቀታቸውን፣ ክህሎታቸውንና አመለካከታቸውን የሚመዝንበት ስልት ነው፡፡
በመሆኑም ተማሪዎች የተማሩትን ትምህርት ይፈተናሉ ሳይሆን ይመዘናሉ በምን ያህል ልኬት ተረድተውታል በሚል ይመዘናሉ እንጂ አይፈተኑም ማለት መጀመር ሳይኖርብን አይቀርም፡፡ በየትምህርት እርከኑ የሚሰጡ ምዘናዎችን የምንወስዳቸው የግድ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ያለንን ደረጃ የምናውቅባቸው መንገዶች መሆናቸውን በመረዳት ከግለሰብ እስከ ተቋማት ድረስ ‘’ምዘናን’’ እና ‘’ፈተናን’’ ነጣጥለን ማየት መጀመር አለብን፡፡ በየትኛውም የትምህርት እርከን ላይ ሆነን ብንገኝ መመዘን ግዴታችን ብቻ ሳይሆን መብታችንም አድርገን ከቆጠርነው ለመመዘን በተቀመጥን ጊዜ የሚሰማን ስጋትም ሆነ መጥፎ ስሜት አይኖርም፡፡ 
የሀገራችን የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ የትምህርት ተደራሽነትን ግብ ባሳከበት መንገድ ጥራትም ላይ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችሉ የትምህርት ስትራቴጂዎች ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ የትምህርት ስትራቴጂዎች የተሳኩ እንዲሆኑ ከሚተገበሩ የማስፈፀሚያ ስልቶች መካከል የትምህርት ምዘና ዋነኛው ነው፡፡ በየትኛውም ደረጃ ይሁን በየትኛውም ጊዜ ከሚሰጡ የትምህርት ምዘናዎች የሚጠበቁ ውጤቶች አሉ፡፡ ለተማሪዎች በርዕሰ ጉዳይም ይሁን በክፍል ደረጃ የሚሰጧቸውን ፈተናዎች እንዲመዝኑ የሚጠበቀው ከዝቅተኛ የትምህርት ቅበላ አቅም አንፃር የተማሪዎችን እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት እንዲሆን ይፈለጋል፡፡ በመሠረታዊነት ሊታወቅ የሚገባውም ይህ ጉዳይ ነው፡፡ የሰዎች ዕውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት በሌሎች ዘንድ ሊታወቅ የሚችልበት ሌላ አግባብ ባለመኖሩ ምክንያት አስፈላጊ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ሁሉ ምዘና ይካሄዳል፡፡ 
በተዘጋጀለት ልክ /Table of Sepacification/ የሚሰጥ ምዘና የሚለካው የተማሪዎችን ዝቅተኛ የዕውቀት መጠን ብቻ አይደለም፡፡ ከዛም ባለፈ ሁኔታ እንደ ሀገር የሚጠበቅበት የጎንዮሽ ጠቀሜታም አለው፡፡ በየደረጃው በሚገኙ የምዘና ውጤቶች አማካኝነት የሚሠሩ ተከታታይ ሥራዎች አሉ፡፡ የተገቢ፣ የአስተማማኝ፣ የፍትሀዊና ሚሥጥራዊነታቸው የተጠበቀ ምዘናዎች ዓላማቸው ተማሪዎች በየደረጃው የሚሰጠውን ትምህርት መቀበል አለመቀበላቸውን ለመመዘን፣ ከአንደኛው የክፍል ደረጃ ወደ ሌላው የክፍል ደረጃ ለሚዘዋወሩ ተማሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት መስጠት፣ የመማር ማስተማሩን ሂደት ለመገምገምና ለማሻሻል የሚረዱ ጠቃሚ መረጃዎችን ለማግኘትና የስርዓተ ትምህርቱን ጥራትና ተገቢነት በተማሪዎች ውጤት አማካኝነት ለሥርዓተ ትምህርት አዘጋጆች፣ ለመምህራን አሰልጣኞች እንዲሁም ለትምህርት መርሀ ግብር አስፈፃሚ አካላት ማመላከት፤ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ከነዚህ የምዘና ዓላማዎች ስንነሳ ለተግባራዊነታቸው ሁሉም አካል የበኩሉን ድርሻ መወጣት እስካልቻለ ድረስ ይሳካሉ ማለት የዋህነት ይሆናል፡፡ 
ምዘናን ተግባራዊ ስናደርግ ማስተሳሰር ያለብን ከሚኖረው ሀገራዊ ፋይዳ ጋር መሆን አለበት፡፡ በአፀደ ህፃናት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከሚሰጡት የትምህርት ምዘናዎች ጀምሮ በየደረጃው የምንገኝ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ትኩረታችንን ልናሳርፍባቸው ይገባል፡፡ ሥራዬ ብለን ምዘናዎቹን መፈተሸ አለብን፡፡ በየደረጃው ከሚሰጡ የክፍል ውስጥ ተከታታይ ምዘናዎች ጀምሮ ሁሉም ምዘናዎች ለህፃናቱና ለታዳጊዎቹ ያስገኙት ፋይዳ ምን እንደሆነ መለካት አለባቸው፡፡ በመደበኛ ትምህርት ሥርዓት ውስጥ የሚሰጡ ምዘናዎች በሚጠበቀው እስታንዳርድ ልክ ስለመሰጠታቸውና የሚለኩት ዕውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት መኖሩን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ የተዘጋጀላቸው የምዘና መርሀ-ግብር /Table of Sepacification/ ስለመኖሩና በዛ መሰረት እየተተገበሩ መሆኑን መከታተል የሁሉም ዜጋ ድርሻ ነው፡፡ እኛ በትምህርት ሂደት ላይ ባንሆን እንኳን የምናስተምረው ልጅ፣ ቤተሰብ፣ ጎረቤትና ነገ በኛ ህልውና ላይ የመወሰን ዕድል ያለው ዜጋ በዚህ ምዘና ውስጥ እንደሚያልፍ መርሳት የለብንም፡፡
ምዘናዎቻችንን መፈተሸና ጥቅምና ጉዳታቸውን ካሉት መለኪያዎች አንፃር መመርመር ያለብን በሀገር አቀፍ ፈተናዎች ላይ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ህፃናት ትምህርት በሚጀምሩበት ወቅት ከሚሰጡ ምዘናዎች ጀምሮ ዓላማቸውን እንዲያሳኩ አድርገን ካዘጋጀናቸው የሀገር አቀፍ ምዘናዎች በሚሰጡበት ወቅት ተማሪዎቻችን ለመመዘን ከመጓጓት ውጭ ምዘናው ፈተና አይሆንባቸውም፡፡ ‘’ተምሬያለሁ መመዘን አለብኝ!’’ የሚል በራሱ የሚተማማን ዜጋ መፍጠር ደግሞ የትምህርት ስርዓቱ ዓላማ በመሆኑ ዓላማው ግቡን እንዲመታ የሚያስችሉ የአመለካከት ክፍተቶቻችንን የሚሞሉ ሥራዎች መከናወን አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካል የሚቆጥበው ጉዳይ ሊኖር አይገባም፡፡
የትምሀርት ምዘና (ፈተና) ሥራ ጉዳይ የትምህርት ሚኒስቴር ወይም የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ብቻ አይደለም፡፡ በዕድሜ፣ በፆታ፣ በብሔርና በሀብት ወ.ዘ.ተ. ክፍፍል ሳይኖር የሁሉም ዜጎች የጋራ ጉዳይ ነው፡፡ የሀገር ህልውና ጉዳይ ያገባኛል የሚል ዜጋ ጥራት ያለው ትምህርት የሚኖረውን ፋይዳ ጠንቅቆ ስለሚረዳ ለተግባራዊነቱ መክፈል ያለበትን መስዋዕትነት በሙሉ ይከፍላል፡፡ የትምህርት ጥራት መሰናክሎችን በየደረጃው ፈልፍሎ በማውጣት የእርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ይመክራል፤ ይዘክራል፡፡ በመሆኑም ዓላማቸውን የሚያሳኩ ምዘናዎች በየደረጃው በሚገኙ የትምህርት ተቋማቶቻችን ውስጥ እንዲሰጡ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል፡፡ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይል እንደ ሀገር ተገቢ የሆነ ውጤታማ ምዘና ተካሂዶ የታለመለትን ግብ እስኪመታ ድረስ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል፡፡