ምን ይጠበቅብኝ ይሆን?

በእያንዳንዱ የትምህርት ቀናት፣ ሳምንታት አልፎም ለወራት በትምህርት ገበታ ላይ ተገኝቶ የተቀሰመን የዕውቀት ልክ በተለያየ መልኩ መመዘን የግድ ይላል፡፡ ይህም ትምህርቱን ሲሰጥ ለነበረው መምህርም ሆነ ሲከታተል የቆየውን ተማሪ የሚገኙበትን ሁኔታ ጠቋሚ በመሆን ሁለቱም በቀጣይ ማስተካከል ያለባቸውን ሁኔታ አመላካች ሆኖ የሚቀጥል ነው፡፡ በዚህም መሰረት ቀለል ካሉ የቃል ጥያቄዎች ጀምሮ እስከ ብሄራዊ ፈተና ድረስ በየደረጃው ምዘናዎች ይካሄዳሉ፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ታዲያ ከወቅቱም ጋር በተያያዘ በብሄራዊ ፈተናዎች ላይ ይሆናል፡፡ እነዚህ ምዘናዎች/ፈተናዎች በሚሰጡበት ወቅት ተማሪዎች ማድረግ ካለባቸው ቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ፈተናው እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ ሊያደርጓቸው የሚገባቸውን ጥንቃቄ በተለያየ ጊዜ መደበኛ በሆነም ሆነ ባልሆነ መንገድ ተደራሽ ሆነዋል፡፡ ከነዚህም መካከል በኤጀንሲያችን አስተባባሪነት በፕላዝማ በተደገፈ መልኩ የሚሰጠው ኦረንቴሽን አንዱ ነው፡፡
በነዚህ የማስተዋወቅ ስራዎች ታዲያ በብሄራዊ ፈተናዎች ወቅት የተፈታኞችን መብትና ግዴታ ማሳወቅ አንዱና ዋነኛው ጉዳይ ተደረጎ ይሰራበታል፡፡ የትምህርት ዘመኑ /የ2010 ዓ/ም/ ምዘና/ፈተና መቃረብ ጋር ተያይዞ የዚህ ጽሁፍ ትኩረትም እንዲሁ በነዚሁ ፈተናዎች ዙሪያ ያጠነጠነ ይሆናል፡፡ ማንኛውም ተማሪ ለፈተናው የሚያደርገውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ለፈተና ሲቀመጥ ያለው መብት እስከምን ድረስ ነው ግዴታውስ? ግዴታውን ባለማክበሩስ የሚወሰድበት የእርምት እርምጃዎች ምን ይመስላሉ? ብሎም ቀላልና ከባድ የምዘና/ የፈተና ደንብ መተላለፍ ችግሮች የምንላቸው የትኞቹን ናቸው? የሚሉትን በተከታታይ የሚዳስስ ይሆናል፡፡
 የተፈታኞች መብት

 ማንኛውም ተፈታኝ በፈተና አሰጣጥ ወቅት መከበር ያለባቸውን ደንቦችና ሥነ-ሥርዓቶች እንዲሁም የፈተና ጥያቄ ጥራዞችና የመልስ ወረቀቶችን አጠቃቀም አስመልክቶ በቂ ገለፃ የማግኘት መብት አለው፣
 ፈተናው በሚሰጥበት ጊዜ ትክክለኛ ያልሆነ የተቀደደ ወይም የተበላሸ የፈተና ጥያቄ ጥራዝ ወይም የመልስ ወረቀት ከገጠመው ወይም በፈተና ወቅት ከተበላሸበት ለፈታኙ በማሳወቅ ሊያስቀይር ይችላል፣
 ለአይነስውራን ተፈታኞች የፈተናውን ጥያቄዎች የሚያነብላቸውና የሚሰጧቸውን መልሶች የሚያጠቁሩላቸው ፈታኞች ለግላቸው ይመደብላቸዋል፣
 የአካል ጉዳት ደርሶበት በራሱ እጅ መፃፍ የማይችል ተፈታኝ የሚያጠቁርለት ሰው በግሉ ይመደብለታል፣
 አንድ ተፈታኝ ፈተናውን በመውሰድ ላይ እያለ የጤና መታወክ ችግር ቢገጥመው ለፈታኙ ችግሩን በመግለፅ እርዳታ ማግኘት ይችላል ሆኖም በማኛውም ምክንያት ለባከነው ጊዜ ተጨማሪ ሰዓት አይፈቀድም፣ 
 ማንኛውም ተፈታኝ የተሰጠውን ፈተና ተረጋግቶ፣ሙሉ ችሎታውንና እውቀቱን ተጠቅሞ እንዳይሠራ የሚያውኩ ሁኔታዎች ከገጠሙት ሰርአቱን ጠብቆ በመጠየቅ መፍትሔ እንዲሰጠው ማሳሰብ ይችላል፣
 ማንኛውም ተፈታኝ በሠራው ስራ ብቻ የፈተና እርማት እንደሚካሔድ በመረዳት የእንደገና ይታይልኝና ይመርመርልኝ ጥያቄ ተቀባይነት እንደማያገኝ አውቆ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ መስራት ይጠበቅበታል፡፡

 የተፈታኞች ግዴታ

 በፈተናው የመጀመሪያ ቀን የጧቱን ክፍለ ጊዜ ፈተና የሚፈተን ማንኛውም ተፈታኝ ፈተናው ከሚጀመርበት ጊዜ አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ በፈተና ጣቢያው ቅጥር ግቢ መገኘትና አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ አለበት፡፡ በሌሎቹ የፈተና ቀናት ፈተናው ከመጀመሩ በፊት ቢያንስ 30 ደቂቃ ቀደም ብሎ በፈተና ጣቢያ ቅጥር ግቢ መገኘት ይኖርበታል፡፡

 ማንኛውም ተፈታኝ ፈተናው ከተጀመረ ከ30 ደቂቃ በኋላ ወደ ፈተና ክፍል እንዲገባ አይፈቀድለትም፡፡ ፈተናው ተጀምሮ 45 ደቂቃ ካልሞላ ፈተናውን ሠርቶ ቢያጠናቅቅም እንዲወጣ አይፈቀድለትም፡፡ ይሁን እንጂ ፈተናው ከተጀመረ ከ45 ደቂቃ በኋላ ከፈተና አዳራሹ ለመውጣት ቢፈልግ በአግባቡ የተፈታኙን ፈቃድ በመጠየቅ የጥያቄ ጥራዝና የመልስ ወረቀቱን ለፈታኙ አስረክቦ በፀጥታ እንዲወጣ ይፈቀድለታል፡፡ በምንም ምክንያት ፈተናው እስኪጠናቀቅ ድረስ የፈተና ጥራዝ ይዞ መውጣት አይፈቀድም፡፡ ሆኖም ፈተናው ሊጠናቀቅ ከ15 ደቂቃ ያላነሰ ጊዜ ሲቀረው የሚጨርስ ተፈታኝ የሁሉም ተፈታኞች የመልስ ወረቀቶች እስኪሰበሰቡና ለፈተናው የተፈቀደው የጊዜ ገደብ አብቅቶ እስኪደወል ድረስ በቦታው በመቆየት የጥያቄ ወረቀቱን ይዞ መውጣት ይችላል፡፡

 አንድ ተፈታኝ የፈተና ጥያቄዎቹን መስራት ከመጀመሩ በፊት በፈተና መልስ ወረቀት ላይ የግል መለያ መረጃዎችን በሙሉ ግልፅ በሆነ ሁኔታ በቅድመ ተከተል መፃፍና በጥንቃቄ ማጥቆር አለበት፡፡

 እያንዳንዱ ፈተና በሚሰጥበት ጊዜ በሚቀርብለት የስም መቆጣጠርያ ላይ በስሙ አንፃር የተመዘገበውን የፈተና ቡክሌት ኮድ ከደረሰው ቡክሌት ኮድ ጋርና በመልስ ወረቀቱ ጫፍ ላይ በፈታኙ ከተፃፈው ቡክሌት ኮድ ጋር መመሳሰሉን አረጋግጦ መፈረም አለበት፡፡ ማንኛውም ተፈታኝ ይህን ባለማድረጉ ለሚፈጠረው ችግር ኃላፊነቱ የራሱ ነው፡፡

 ማንኛውም ተፈታኝ የራሱ ችሎታና እውቀት ተጠቅሞ፤ የሚሰራባቸው የጥያቄና የመልስ ወረቀቶች ለሌሎች ተፈታኞች ዕይታ የተጋለጡ እንዳይሆኑ ሽፍኖ መስራት ይኖርበታል፡፡ ለሌሎች ተፈታኞች ድጋፍ መስጠት ሆነ ከሌሎች መቀበል ፈፅሞ የተከለከለ ነው፡፡

 ከባድና ቀላል የፈተና ደንብ መተላለፍ ችግሮችና 
የሚያስወስዱት እርምጃዎች …….  (ይቀጥላል)