ምን ይጠበቅብኝ ይሆን? … የቀጠለ

የደንብ መተላለፍ ችግሮችና የሚያስወስዱት እርምጃዎች
• በስሙና በተሰጠው የምዝገባ ቁጥር ሌላ ሰው ያስፈተነ ወይም በሌላ ሰው ስምና ምዝገባ ቁጥር የተፈተነ፣
• በፈታኝ የሚሰጠውን ምክርና ተግሳፅ ባለመቀበል ሶስትና ከሶስት በላይ ፈተናዎች/የፈተና ክፍለ ጊዜዎች /ተደጋጋሚ ጥፋቶች መፈፀሙ ሪፖርት የተደረገበት፣ 
• ከራሱ ፈተና ውጪ ለሌላ ተፈታኝ መልስ የሠራ ፣
• ፈታኝን የሠደበ፣ በፈታኝ ላይ የዛተና ለመደብደብ የሞከረ፣
• የሌላን ተፈታኝ የፈተና ወረቀት (Booklet) ወይም የመልስ ወረቀት የቀማ ወይም ለመቀማት የሞከረ፣
• በፈተና ክፍል ውስጥ ሌላውን ተፈታኝ ፈተናውን ተረጋግቶ እንዳይሰራ ያወከና ማናቸውንም ዓይነት የሃይል ወይም የጉልበት ተግባር የፈፀመ፣
• በፈተና ወቅት የፈተና ጥያቄ ወረቀቱን ከፈተና ክፍል ውጭ እንዲወጣ ለማድረግ የሞከረ ወይም ያወጣ፣
• ሌሎች ተፈታኞችን በማሳደም የፈተና ክፍሉንም ሆነ የፈተና ጣቢያውን ሰላም በማወክ የፈተናውን ሂደት ለማስተጓጎል የሞከረ፣
• ለፈተና እንዲቀመጥ የሚያስችለውን የዓመቱን ትምህርት ያላጠናቀቀ፣
• በፈተና ክፍል ውስጥ ሞባይል ይዞ የተገኘ፣
• የዩኒቨርሲቲ መግቢያ /የ12ኛ ክፍል/ ፈተና ተፈታኝ ሆኖ ለ10ኛ ክፍል ሲፈተን የተያዘ ተማሪ የተፈተናቸው ፈተናዎች ውጤቶች ከመሰረዛቸውም በላይ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናውንም እንዳይፈተን ይደረጋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፡- 
 መኮራረጅ/ሁለት ወይም ከሁለት በላይ ሆነው ፈተናውን በጋራ መስራት፣
 ከውጭ ተሰርቶ የገባ መልስ ተጠቅሞ ፈተናው መስራት፣
 ሆን ብሎ የፈተና መልስ ማስቀዳት /መንገር ወይም በብጣሽ ወረቀት ጽፎ ለሌላ ተፈታኝ ማስተላለፍ ወይም የሠራበትን የፈተና ቡክሌት ለሌላ ሰው መስጠት፣
 የፈተና መልስ ከሌላ ተፈታኝ መቅዳት ወይም መልስ የተፃፈበት ብጣሽ ወረቀት ይዞ መገኘት ወይም ከሌላ ተፈታኝ መልስ የተሰራበት የፈተና ቡክሌት መቀበል፣
 ፈታኙ በመልስ ወረቀቱ አናት ላይ የፃፈውን የቡክሌት ኮድ መለወጥ፣
 አጫጭር ፎርሙላዎችንና ማስታወሻዎችን በብጥስጣሽ ወረቀቶች ወይም በሌላ መልክ ይዞ በፈተና አዳራሽ ውስጥ መገኘት፣
 በስሙና በምዝገባ ቁጥሩ በአንድ የትምህርት ዓይነት ፈተና ሁለት የመልስ ወረቀቶች ተሰርቶ መገኘት፣
 የፈተና መልስ መስጫ ወረቀቱን ሆነ ብሎ ማበላሸት ወይም መቅደድ፣
 አንድ ተፈታኝ ወደ ፈተና አዳራሽ ይዞ መግባት ከሚፈቀድለት የጽሕፈት መሳሪያ ማለትም እርሳስ፣ ላፒስ ማስመሪያና መቅረጫ ውጭ የተከለከሉ እንደ ካልኩሌተር የመሳሰሉትን የኤሌክትሮሊክስ መሳርያዎች ይዞ ወደ ፈተና አዳራሽ መግባት፣
 በራሱ ፈቃድና በእምቢተኝነት ፈታኙ ከመደበው ቦታ/መቀመጫ/ሌላ ቦታ ቀይሮ መገኘት፣
 በፈተና ጣቢያ ኃላፊው ወይም በረዳቱ በኩል የተደረገ የጊዜ ለውጥ ስለመኖሩ እስካልተገለፀ ድረስ አንድ ተፈታኝ የተፈቀደውን የጊዜ ገደብ ማክበር ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ውጭ ለፈተና የተሰጠው የጊዜ ገደብ አለማክበር፣
 ስካርቭ፣ባርኔጣ/ቆብ፣ሻሽና የመሳሰሉት አድርጎ /ለብሶ ወደ ፈተና አዳራሽ መግባት በፍፁም የተከለከለ ነው፡፡ ይሁንና በሃይማኖታዊና ባህላዊ ህጎች አስገዳጅነት ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ሙሉ የፊት ገጽታና ሁለቱም ጆሮዎች ያልሸፈነ መሆን አለበት፡፡ይህንን መመሪያ አክብሮ አለመገኘት፣
ከላይ ከተጠቀሱት ጥፋቶች አቻ /ተመሳሳይ የሆኑ ሌሎች የደንብ መተላለፍ ችግሮችን የፈፀመ ተፈታኝ ከፈተና ክፍል /አዳራሽ ተወግዶ ሕገ ወጥ ደርጊት ሲፈፅም የተገኘበት የፈተና ውጤት ብቻ ይሰረዛል፡፡ በሌሎች የፈተና ጊዜያቶች ተገቢውን ህግ በማክበር በፈተና ላይ መቀመጥ ይችላል፡፡ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩ የፈተና ደንብ መተላለፍ ችግሮችና ቅጣቶቻቸው እንደተጠበቁ ሆነው፡-
 በፈተና አሰጣጥ ወቅት በጣቢያው የሥነ-ሥርዓት ጉድለት እንደተፈፀመና ፈተና በሕገ-ወጥ መንገድ በግል፣በቡድን በክፍል ደረጃ ወይም በፈተና ጣቢያ ደረጃ እንደተሰራ የሚጠቁም ማንኛውም መረጃ ከተገኘ ወይም በፈተና ውጤት መጋሸብ/መናገር መነሻነት ጉዳዩ በኤጀንሲው ሲረጋገጥ በጣቢያው ያሉ ተፈታኞች ውጤት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝና ውሳኔውን የሚመለከታቸው አካላት በጹሑፍ እንዲያውቁት ይደረጋል፣
 በማንኛውም ደረጃ በመማር ላይ ያለ አንድ ግለሰብ ለሌላ ሰው ሲፈተን ከተገኘ በሕግ አግባብ የሚጠየቅ ከመሆኑም በተጨማሪ ለአንድ ዓመት ከትምህርቱ እንዲታገድ ይደረጋል፣
 ከላይ ከተዘረዘሩት ከፍተኛ የፈተና ደንብ መተላለፍ ችግሮች አንፃር አቻ/እኩል ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች የፈተና ደንብ መተላለፍ ችግሮችን በፈፀመ ተፈታኝ ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ከላይ የተጠቀሱት የቅጣት እርምጃዎች ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡
በመሆኑም ተፈታኞች ለአመታት የደከሙበትን ውጤት በነዚህ የፈተና ደንብ መተላለፍ ችግሮች የተነሳ እንዳያጡ ፈተናቸውን በጥንቃቄና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲሰሩና የሚገባቸውን ውጤት በማስመዝገብ ወደ ቀጣዩ የትምህርት እርከን እንዲሸጋገሩ የራሳቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል፡፡
አሁንም በድጋሚ መልካም የዝግጅት ጊዜ እንመኛለን!